የመካ – ጧኢፍ ጉዞ
በሚቀጥለው ዓመት በዙልሒጃ ወር እንደገና ለመምጣት አስበው ወደ አገራቸው ለመመለስ ከነብያችን ፈቃድ ጠይቀው ተለዩ። እነዚህ አዲስ ሙስሊሞች የሆኑት ስድስቱ ሰዎች ዑቅባ ኢብኑ ዓሚር፣ አስዐድ ኢብኑ ዙራራ፣ ዐውፍ ኢብኑል ሐሪስ፣ ራፊዕ ኢብኑ ማሊክ፣ ቁጥባ ኢብኑ ዓሚርና ጃቢር ኢብኑ ዐብዱላህ (ረዲየላሁ ዐንሁም) ነበሩ።1
ሙስሊም የሆኑት ስድስቱ ሰዎች ወደ መዲና ወደ ሕዝባቸው በተመለሱ ጊዜ ወዲያውኑ ስለ እስልምናና ስለ ነብያችን መናገር ጀመሩ፤ ሕዝቡንም ወደ እስልምና ሃይማኖት እንዲገባ መጥራት ጀመሩ። በዚህም እስከዚያ ድረስ ገፉበት፤ በመዲና ስለ ነብያችንና ስለ እስልምና የማይነገርበት አንድም ቤት አልቀረም። በዚህም እስልምና በኸዝረጅ ጎሳ መካከል እንደተስፋፋው ሁሉ ከአውስ ጎሳም አንዳንድ ሰዎች ሙስሊሞች ሆኑ።
የጧኢፍ ሰዎችን ወደ ኢማን መጥራታቸው
አጋሪዎቹ ከውዱ ነብያችን እጅግ ብዙ ተአምራትን ቢያዩም ከግትርነታቸው የተነሣ አላመኑም፤ ከዚህም በላይ ሙስሊም የሆኑትን ልጆቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውን፣ ዘመዶቻቸውንና ጓደኞቻቸውን ከማሰቃየትና ከመበደል አልተቆጠቡም። እየበረታ በሄደው በዚህ ግፍና ስቃያቸው ውዱ ነብያችን እጅግ አዘኑ። በመካ አቅራቢያ ወደምትገኘው ወደ ጧኢፍ ሄደው ሕዝቧን ወደ እስልምና ለመጥራት አሰቡ። ስለዚህ ዘይድ ኢብኑ ሐሪሳን ይዘው ወደ ጧኢፍ ሄዱ።
ከጧኢፍ ታላላቆች ከሆኑት ከዐምር ልጆች፣ ከዐብዱ ያሊል፣ ከሐቢብና ከመስዑድ ጋር ተነጋገሩ። እስልምናን አስረድተው በአላሁ ተዓላ እንዲያምኑ ጠየቋቸው። እነርሱ ግን አላመኑም፤ እንዲያውም ሰደቧቸው፤ ከዚህም በላይ እንዲህ አሉ፦ «አላሁ ተዓላ ነብይ አድርጎ ለመላክ ከአንተ ሌላ ማንንም አላገኘምን? አላሁ ተዓላ ከአንተ ሌላ ሰውን ነብይ አድርጎ መላክ ይሳነዋልን? ከአገራችን ውጣና ወደፈለግከው ሂድ!.. ወገንህ የምትለውን ስላልተቀበለ አይደለምን ወደዚህ የመጣኸው? እኛም ከአንተ እንደምንርቅ እንምላለን። አንዲቱንም ጥያቄህን አንቀበልም።»
ክቡር ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በሐዘን ከእነርሱ ዘንድ ተለዩ። የሰቂፍን ጎሳ ለአሥር ቀን ወይም ለአንድ ወር ወደ እስልምና ጠሩ፤ ነገር ግን ከእነርሱ አንድም ሰው አላመነም፤ ይልቁንም አፌዙባቸው፣ አሰቃዩአቸው፣ ጮኹባቸውም። ሕፃናትንና ወጣቶችን በሚያልፉበት መንገድ ዳር አሰልፈው በድንጋይ አስወገሯቸው፤ በእርሳቸውም ላይ አስነሡባቸው። ሰይዲና ዘይድ የጧኢፍ ወጣቶች የሚወረውሯቸውን ድንጋዮች ሰውነታቸውን ጋሻ አድርገው በመመከት በነብያችን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ይሞክሩ ነበር። ሰይዲና ዘይድ በውዱ ነብያችን ዙሪያ ይሽከረከሩ ነበር፤ ድንጋዮቹ እንዳይነኳቸው ይውተረተሩ ነበር። በተባረከ አካላቸው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሲሉ ወደ ራሳቸው የሚመጡትን ድንጋዮች ከቁብ አይቆጥሩም ነበር። ሕይወታቸውን በእንዲህ ያሉ ቀናት ለመሠዋት ዕድል ይጠባበቁ አልነበረምን? እነሆ የዓለማትን ሰይድ በድንጋይ እየወገሩ፣ እያሰቃዩና እያንገላቱ ከአገራቸው ሊያስወጧቸው ይሞክሩ ነበር።
ሰይዲና ዘይድ ክቡር ነብያችንን ለመጠበቅ ወደ ቀኝና ወደ ግራ በሮጡ ቁጥር ድንጋዮቹ ራሳቸውን፣ ሰውነታቸውንና እግሮቻቸውን አንዱ ሌላውን እየተከተለ ይመቷቸው ነበር። በዚህ ምክንያት ሰይዲና ዘይድ ሁለንተናቸው በደም ተለወሰ። ውዱ ነብያቸውን ለመጠበቅ ያላቸውን ሁሉ ይሰጡ ነበር፤ ድንጋይ በሚወረውሩት ግፈኞች ላይ ድምፃቸው እስከቻለ ድረስ እንዲህ እያሉ ይጮኹ ነበር፦ «ተዉ!.. አትምቱ!.. እርሳቸው የዓለማት ሰይድ ናቸው! እርሳቸው ረሱሉላህ ናቸው!.. ሰውነቴን ቆራርጡት፤ ነገር ግን በነብያችን ላይ ጉዳት አይድረስ!..» ዘይድ ኢብኑ ሐሪሳን አልፈው ወደ ክቡር ረሱሉላህ የደረሱት ድንጋዮች የሰይዳችንን የተባረኩ እግሮች በደም አጥለቅልቀው ነበር።
ውዱ ነብያችን ያዘኑ፣ የደከሙና የቆሰሉ ሆነው ዑትባና ሸይባ የተባሉ የሁለት ወንድማማቾች የወይን አትክልት ቦታ ተጠጉ። በዚያም ምእመናን ሁሉ ሕይወታቸውን ሊሠዉላቸው የሚሹት ክቡር ረሱሉላህ ከተባረኩ እግሮቻቸው የሚፈሰውን ደም ጠረጉ።
ውዱእ አድርገው በዛፍ ሥር ሁለት ረከዓ ሶላት ሰገዱ። ከዚያም የተባረኩ እጆቻቸውን አንሥተው ወደ ጌታቸው መማጸን ጀመሩ።
የአትክልቱ ባለቤቶች ይህን ሁኔታ ይመለከቱ ነበር። በክቡር ረሱሉላህ ላይ የደረሰውን አይተው ነበር፤ የብቸኝነታቸውም ምስክሮች ሆነው ነበር። ርኅራኄያቸው ተቀሰቀሰ። ዐዳስ በተባለው ባሪያቸው በኩል ወይን ላኩላቸው። ውዱ ነብያችን ወይኑን ሲበሉ ቢስሚላህ አሉ። ወይኑን ያመጣው ባሪያ ክርስቲያን ነበር። ቢስሚላህን በሰማ ጊዜ ተገርሞ፦ «ለዓመታት እዚህ አካባቢ ኖሬያለሁ፤ ከማንም እንዲህ ያለ ቃል አልሰማሁም። ይህ ምን ዓይነት ቃል ነው?» ብሎ ጠየቀ።
ረሱሉላህ፦ «አንተ ከየት ነህ?» አሉ። ዐዳስ፦ «የነነዌ ሰው ነኝ» አለ። ረሱሉላህ፦ «ለካ ከዩኑስ (ዐለይሂ ሰላም) አገር ነህ» አሉ። ዐዳስ፦ «ዩኑስን ከየት ያውቋቸዋል? በዚህ አካባቢ ማንም አያውቃቸውም» አለ። ረሱሉላህ፦ «እርሳቸው ወንድሜ ናቸው። እርሳቸውም እንደ እኔ ነብይ ነበሩ» አሉ።
ዐዳስ፦ «የዚህ ውብ ፊትና የእነዚህ ጣፋጭ ቃላት ባለቤት ውሸታም ሊሆን አይችልም። እርስዎ የአላህ መልዕክተኛ መሆንዎን አምኛለሁ» አለ። ሙስሊም ሆኑ፤ እንዲህም አሉ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ለዓመታት ለእነዚህ ግፈኞች፣ ለእነዚህ ውሸታሞች ባሪያ ሆኜ ኖርኩ። የሁሉንም ሐቅ ይበላሉ። ሁሉንም ያታልላሉ። ምንም መልካም ገጽታ የላቸውም። ዓለማዊ ነገር ለመሰብሰብና ፍትወታቸውን ለማርካት ማንኛውንም ዝቅተኛ ተግባር ከመፈጸም አይመለሱም። እጠላቸዋለሁ። ከእርስዎ ጋር መሄድ፣ እርስዎን በማገልገል መከበር፣ መሃይማንና ሞኞች በእርስዎ ላይ ለሚያደርጉት ንቀት ዒላማ መሆንና የተባረከ አካልዎን ለመጠበቅ ራሴን መሠዋት እፈልጋለሁ።»2
ክቡር ረሱሉላህ ፈገግ ብለው፦ «አሁን በአሳዳሪዎችህ ዘንድ ቆይ! በቅርቡ ስሜን በየቦታው ትሰማለህ። ያን ጊዜ ወደ እኔ ና» አሉ።
«ተዉ!.. አትምቱ!.. እርሳቸው የዓለማት ሰይድ ናቸው! እርሳቸው ረሱሉላህ ናቸው! ሰውነቴን ቆራርጡት፤ ነገር ግን በነብያችን ላይ ጉዳት አይድረስ!» ዘይድ ኢብኑ ሐሪሳ (ረዲየላሁ ዐንሁ)
ጥቂት ዕረፍት ካደረጉ በኋላ ወደ መካ ጉዞ ጀመሩ። ወደ መካ የሁለት ማረፊያ ርቀት ሲቀራቸው አንድ ደመና ጥላ እንደሚያጠላላቸው አዩ። በትኩረት ሲመለከቱ ጂብሪል ዐለይሂ ሰላም መሆናቸውን ተረዱ። ይህን ክስተት ውዱ ነብያችን ለእናታችን ዓኢሻ ሲዲቃ ተርከውላቸው ነበር።
በ«ሶሒሕ ቡኻሪ» እና በአሕመድ ኢብኑ ሐንበል «ሙስነድ» እንደተዘገበው፣ አንድ ቀን እናታችን ሰይደቲና ዓኢሻ፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ከኡሑድ ቀን የበለጠ አሳማሚ ቀን አጋጥሞዎት ያውቃልን?» ብለው ጠየቁ፤ ክቡር ረሱሉላህም እንዲህ ብለው መለሱ፦ «በአላህ እምላለሁ፤ በኡሑድ ጦርነት ከነበሩት ከሓዲዎች እንኳ ያልደረሰብኝን ያህል ስቃይ ከወገንሽ ደረሰብኝ። ራሴን ለኢብኑ ዐብዱ ያሊል ኢብኑ ዐብዱ ኩላል ባቀረብኩ ጊዜ (ማለትም ነብይነቴን አሳውቄ ወደ ሃይማኖት በጠራሁት ጊዜ) አልተቀበለም። ከእነርሱ ዘንድ በዚህ ያህል ታላቅ ስቃይ ተለየሁ፤ ቀርኑ ሠዓሊብ ወደሚባለው ስፍራ እስክደርስ ድረስ ራሴን አላወቅሁም። በዚያ ራሴን ወደ ላይ አነሣሁ። አንድ ደመና ጥላውን በላዬ እንደዘረጋ አየሁ። ስመለከት በደመናው ውስጥ ጂብሪል (ዐለይሂ ሰላም) ቆመው ነበር። ጠሩኝና እንዲህ አሉ፦ ‹ሙሐመድ ሆይ! ሐቅ ተዓላ ወገንዎ ስለ እርስዎ የተናገሩትን ሰማ። ሊጠብቁዎት እንዳልፈለጉም ያውቃል። የፈለጉትን እንዲያዙት በተራሮች ላይ የተሾመውን ይህን መልአክ ወደ እርስዎ ላከ።› ያም መልአክ ጠርቶኝ ሰላምታ ካቀረበልኝ በኋላ እንዲህ አለ፦ ‹ሙሐመድ ሆይ! ጂብሪል እንዳሉት ሐቅ ተዓላ የፈለጉትን እንዲያዙኝ የተራሮች መልአክ የሆንኩትን እኔን ወደ እርስዎ ላከኝ። ለትእዛዝዎ ዝግጁ ነኝ። እነዚህ ሁለት ቀጥ ያሉ ተራሮች (የቁዐይቂዓን ተራራና የአቡ ቁበይስ ተራራ) በመካ ሰዎች ላይ እስኪደፉ ድረስ እንዲገናኙ (አጋሪዎቹንም ሙሉ በሙሉ እንዲደፈጥጡ) ከፈለጉ ያዝዙ፤ አገናኛቸዋለሁ።› እኔ አልተስማማሁም፤ እንዲህም አልኩ፦ ‹(አይሆንም! እኔ ለዓለማት እዝነት ሆኜ ተልኬያለሁ።) አላሁ ተዓላ ከእነዚህ አጋሪዎች ዘር ክብሩ የላቀውን አላህን ብቻ የሚያመልክና በአላሁ ተዓላ ምንም ነገር የማያጋራ ትውልድ እንዲያስገኝ ዱዓ አደርጋለሁ።›»
ክቡር ነብያችን ከጧኢፍ ወደ መካ ሲመለሱ ነኽላ በሚባለው ስፍራ ጥቂት ዕረፍት አደረጉ። በአንድ ወቅት ሶላት ላይ ቆመው ነበር። ከኑሰይቢን ጂኖች አንድ ቡድን በዚያ ሲያልፍ ውዱ ነብያችን የሚያነቧቸውን የቁርኣን ከሪም አንቀጾች ሰምቶ ቆመና አዳመጠ። ከዚያም ከክቡር ነብያችን ጋር ተነጋግረው ሙስሊሞች ሆኑ። ክቡር ነብያችንም፦ «ወደ ወገናችሁ በደረሳችሁ ጊዜ ወደ ኢማን የማደርገውን ጥሪዬን ለእነርሱም ንገሯቸው። እነርሱንም ወደ ኢማን ጥሯቸው» አሏቸው።
እነዚያ ጂኖች ወደ ወገናቸው ሄደው ይህን ባሳወቁ ጊዜ የሰሙት ጂኖች ሁሉ አመኑ።3 ይህ በቁርኣን ከሪም በሱረቱ አል-ጂን፣ እንዲሁም «ቡኻሪ» እና «ሙስሊም» በሚባሉት የታወቁ የሐዲስ ሸሪፍ መጻሕፍት ተዘግቧል።
ወደ መካ በተቃረቡ ጊዜ ምእመናን ለክቡር ረሱሉላህ፦ «ቁረይሾች የጧኢፍ ወራዳዎች በእርስዎ ላይ ያደረሱትን መጥፎ አያያዝ ሰምተዋል። አሁን ቢመጡ ግፋቸውን ሊያበዙ ይችላሉ» ብለው መልእክት ላኩ። ክቡር ነብያችን ሒራ በደረሱ ጊዜ አንድ ሰው ወደ ሱሀይል ኢብኑ ዐምር ልከው በጥበቃው ሥር እንዲያደርጋቸው ጠየቁ። ያ ዕድለ ቢስ እምቢ ባለ ጊዜ ወደ ሙጥዒም ኢብኑ ዐዲይ መልእክት ላኩ። እርሱም ይህን ልመና ተቀበለ። ሐቢቡል አክረምና የተከበሩት ነብይ በሙጥዒም ኢብኑ ዐዲይ ጥበቃ ሥር ወደ መካ መጡ። ሙጥዒምም ይህን ሁኔታ ለቁረይሾች አሳወቀ። ረሱሉላህ በይቱ ሸሪፍን ጠዋፍ አድርገው ሐጀሩል አስወድን ሳሙ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ሙጥዒምን፦ «ከዚህ በላይ በአንተ ጥበቃ ሥር አልቆይም» አሉት። ሙጥዒምም ተቀበለ። ክብሩ የላቀው አላህ ሐቢቡን በራሱ ጥበቃ ሥር ጠበቀ።
«ላ ኢላሀ ኢለላህ» በሉና ዳኑ
መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም ሰዎችን ወደ እውነተኛው መንገድ መጥራታቸውን ቀጠሉ። በዚህ ጊዜ አጋሪዎቹ እንደገና ገደባቸውን አልፈው ከቀድሞው የበለጠ ማሰቃየትና መበደል ጀመሩ። በዚህ ምክንያት ክብሩ የላቀው አላህ ክቡር ነብያችንን ካዕባ በሚጎበኝበት ወቅት ለጉብኝት ከሚመጡ የዓረብ ጎሳዎች ጋር እንዲነጋገሩና ወደ እስልምና እንዲጠሯቸው አዘዘ። ውዱ ነብያችን በዚህ ትእዛዝ መሠረት በመካ ዙሪያ ወደሚቆሙት ወደ ዙል መጃዝ፣ ዑካዝና መጀና ገበያዎች መሄድ ጀመሩ።
ወደዚያ በተደጋጋሚ እየሄዱ ጎሳዎቹን ወደ አላሁ ተዓላ አንድነትና እርሱን ወደ ማምለክ ይጠሩ ነበር፤ ነብይ መሆናቸውንም እንዲቀበሉ ይነግሯቸው ነበር። ከተቀበሉ ክብሩ የላቀው አላህ ጀነትን እንደሚሰጣቸው ያሳውቁ ነበር። የሚያሳዝነው ክቡር ነብያችን በልመና መልክ ለሚያደርጉት ለዚህ ጥሪ ማንም ጆሮ አልሰጠም፤ አንዳንዶቹ ብልግና ያሳዩ፣ ይሰድቡ ነበር፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ፊታቸውን አጨፍግገው መጥፎ ቃላት ይናገሩ ነበር። የቁረይሽ አጋሪዎችም እርሳቸውን እየተከተሉ የሄዱባቸውን ጎሳዎች ያበላሹ ነበር።
ኢማም አሕመድ፣ በይሀቂ፣ ጠበራኒና ኢብኑ ኢስሓቅ እንዳሳወቁት ረቢዓ ኢብኑ ዐባድ እንዲህ ብለው ዘገቡ፦ «ወጣት ነበርኩ። ከአባቴ ጋር ወደ ሚና ሄደን ነበር። መልዕክተኛው ዐለይሂ ሰላም የዓረብ ጎሳዎች ወደሰፈሩበት ስፍራ እየሄዱ እንዲህ ይሉ ነበር፦ ‹እናንተ የእገሌ ልጆች ሆይ! እኔ የምታመልኳቸውን እነዚህን ጣዖታት ጥላችሁ በአላሁ ተዓላ ምንም ሳታጋሩ እንድታመልኩት፣ በእኔ እንድታምኑና እውነተኛነቴን እንድታረጋግጡ፣ ከሐቅ ተዓላ ዘንድ የተላክሁበትን ተግባር እስካብራራውና እስክፈጽመው ድረስ እንድትጠብቁኝ የሚያዛችሁ የአላሁ ተዓላ መልዕክተኛ ነኝ!…›
ከኋላቸው የሚሄድ ዓይነ ሸውራራ፣ ጸጉሩን የጎነጎነ አንድ ሰው ደግሞ፦ ‹እናንተ የእገሌ ልጆች ሆይ! ይህ ሰው ጣዖቶቻችንን ላትንና ዑዛን ከማምለክ ከልክሎ ራሱ ወደፈጠረው ሃይማኖት ይጠራችኋል!.. ተጠንቀቁ! አትስሙት፤ አትታዘዙትም!..› ይል ነበር። እኔም አባቴን፦ ‹እርሳቸውን የሚከተለው ይህ ሰው ማን ነው?› ብዬ ጠየቅሁ። ‹አጎታቸው አቡ ለሀብ ነው› አለኝ።»
ጠበራኒ ከጧሪቅ ኢብኑ ዐብዱላህ እንዲህ ብለው ዘገቡ፦ «መልዕክተኛውን ዐለይሂ ሰላም በዙል መጃዝ ገበያ አይቻቸው ነበር። ሰዎች እንዲሰሟቸው በታላቅ ድምፅ፦ ‹እናንተ ሰዎች ሆይ! «ላ ኢላሀ ኢለላህ» (ከአላሁ ተዓላ በስተቀር አምላክ የለም) በሉና ዳኑ!› እያሉ ይጣሩ ነበር። እርሳቸውን የሚከተል አንድ ሰው ደግሞ በእጁ ያገኛቸውን ድንጋዮች ወደ እግሮቻቸው እየወረወረ፦ ‹እናንተ ሰዎች ሆይ! አትመኑት!.. ከእርሱ ተጠንቀቁ! ምክንያቱም እርሱ ውሸታም ነው!..› ይል ነበር። የሚመቷቸው ድንጋዮች የተባረኩ እግሮቻቸውን አድምተው ነበር፤ እርሳቸው ግን አሁንም ሳይሰለቹና ሳይታክቱ ጥሪያቸውን ይቀጥሉ ነበር። ‹ይህ ወጣት ማን ነው?› ብለው ጠየቁ። አንድ ሰው፦ ‹ከዐብዱልሙጠሊብ ልጆች አንድ ወጣት ነው› ብሎ መለሰ። ‹ድንጋይ የሚወረውረውስ ማን ነው?› ብለው ሲጠይቁ፦ ‹አጎቱ አቡ ለሀብ ነው› አለ።»
ኢማም ቡኻሪ «አት-ታሪኹል ከቢር» በተባለው መጽሐፋቸው፣ ጠበራኒም «አል-ሙዕጀሙል ከቢር» በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ብለው ጠቅሰዋል፦ ሙድሪክ ኢብኑ ሙኒብ ከአባታቸው፣ አባታቸውም ከአያታቸው እንዲህ ብለው ዘገቡ፦ «ከአባቴ ጋር ወደ ሚና መጥተን ሰፍረን ነበር። አንድ ጉባኤ አጋጠመን። አንድ ሰው ለእነርሱ፦ ‹እናንተ ሰዎች ሆይ! ላ ኢላሀ ኢለላህ በሉና ዳኑ!› ይሉ ነበር። በዙሪያቸው ካሉት ሰዎች አንዳንዶቹ በዚያ ውብ ፊታቸው ላይ ይተፉ ነበር፤ አንዳንዶቹ በራሳቸው ላይ አፈር ይበትኑ ነበር፤ አንዳንዶቹ ደግሞ እየረገሙ ልዩ ልዩ ስድብ ይሰድቡ ነበር። ይህ ሁኔታ እስከ ቀትር ድረስ ቀጠለ። በዚህ ጊዜ አንዲት ልጃገረድ በእጇ የውኃ ዕቃ ይዛ ወደዚያ መጣች። እርሳቸውን በዚያ ሁኔታ ባየች ጊዜ ማልቀስ ጀመረች። እርሳቸውም ውኃ ከጠጡ በኋላ ወደ ልጅቱ ዘወር ብለው፦ ‹ልጄ ሆይ! አባትሽ በወጥመድ ተይዞ ይገደላል፣ ይዋረዳል ብለሽ አትፍሪ!› አሉ። ከዚያም እኛ በዚያ የነበሩትን፦ ‹ይህ ሰውና ያቺ ልጅ እነማን ናቸው?› ብለን ጠየቅን። ‹ይህ ከዐብዱልሙጠሊብ ልጆች የሆኑት ሙሐመድ ናቸው፤ አጠገባቸው ያለችውም ልጃቸው ዘይነብ ናት› አሉ።»
«እርሳቸው (ዩኑስ ዐለይሂ ሰላም) ወንድሜ ናቸው። እርሳቸውም እንደ እኔ ነብይ ነበሩ» ሐዲስ ሸሪፍ
ሰዒድ ኢብኑ የሕያ ኢብኑ ሰዒድ አል-ኡመዊ «መጋዚ» በተባለው መጽሐፋቸው ከአባታቸው ዘገቡ፤ አባታቸውም ከአቡ ኑዐይምና ከዐብዱረሕማን አል-ዓሚሪ፣ ዐብዱረሕማን አል-ዓሚሪም ከብዙ ሰዎች ዘገቡ። እንዲህ አሉ፦ አንድ ቀን ውዱ ነብያችን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ወደ ዑካዝ ገበያ ሄዱ። ወደ በኑ ዓሚር ጎሳ ሄደው፦ «እናንተ በኑ ዓሚር ሆይ! ወደ እናንተ የሚጠጋውን ሰው እንዴት ትጠብቃላችሁ?» ብለው ጠየቋቸው። እነርሱም፦ «ማንም በእኛ ላይ ክፉ ቃል ሊወረውር አይችልም፤ ማንም ሳናውቅ በእሳታችን ሊሞቅ አይችልም!..» አሉ። ክቡር ነብያችን፦ «እኔ የአላሁ ተዓላ መልዕክተኛ ነኝ። ወደ እናንተ ብመጣ ጌታዬ የሰጠኝን የነብይነት ተግባር ለሰዎች እስካደርስ ድረስ ትጠብቁኛላችሁን?» አሉ። እነርሱም፦ «አንተ ከቁረይሽ ከየትኞቹ ነህ?» ብለው ጠየቁ። ሰይዳችን፦ «ከዐብዱልሙጠሊብ ልጆች ነኝ» ባሉ ጊዜ፦ «ከዐብዱልሙጠሊብ ልጆች ከሆንክ ታዲያ ለምን አይጠብቁህም?» አሉ። ክቡር ረሱሉላህም፦ «እኔን ከሚያስተባብሉት ቀዳሚዎቹ እነርሱ ሆኑ» አሉ። የበኑ ዓሚር ጉባኤም እንዲህ አሉ፦ «ሙሐመድ ሆይ! እኛ አንተን አንቃወምም፤ ያመጣኸውንም አናምንም። ነገር ግን የነብይነት ተግባርህን ለሰዎች እስክታደርስ ድረስ እንጠብቅሃለን።»
በዚህ ጊዜ ክቡር ነብያችን በአጠገባቸው ተቀመጡ። በዚያን ወቅት ከበኑ ዓሚር ታላላቆች አንዱ የሆነው በይሐራ ኢብኑ ፋሪስ በገበያው ግብይቱን ጨርሶ ወደ እነርሱ መጣ፤ ክቡር ነብያችንን እያመለከተ በዚያ የነበሩትን፦ «ይህ ማን ነው?» ብሎ ጠየቀ። እነርሱም፦ «ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱላህ ነው» አሉ። በይሐራ፦ «በአጠገባችሁ እስክታስቀምጡት ድረስ ከእርሱ ጋር ምን ጉዳይ አላችሁ?» ባለ ጊዜ፦ «ወደ እኛ ተጠግቷል፤ የአላህ መልዕክተኛ እንደሆነ ይናገራል፤ የነብይነት ተግባሩን ለሰዎች እስኪያደርስ ድረስ እንድንጠብቀውም ይጠይቃል» አሉ። በዚህ ጊዜ በይሐራ ወደ ክቡር ነብያችን ዘወር ብሎ፦ «አንተን ለመጠበቅ መነሣታችን ደረታችንን ለዓረቦች ሁሉ ቀስት ዒላማ ማድረግ ማለት ነው» አለ። ሕዝቡንም እንዲህ አለ፦ «ወደ አገሩ ከእናንተ የከፋ ነገር ይዞ የሚመለስ ጎሳ የለም። እንግዲህ እናንተ ከዓረቦች ሁሉ ጋር ልትዋጉ፣ ሰውነታችሁንም ለቀስታቸው ዒላማ ልታደርጉ ነው!.. ወገኑ በእርሱ ዘንድ መልካም ነገር ቢያይ ኖሮ በመጀመሪያ ራሳቸው በጠበቁት ነበር። እናንተ ወገኑ አስተባብሎ ከአጠገቡ ያራቀውን ሰው ልታስጠልሉና ልትረዱ ተነሣችሁ!.. እጅግ ተሳስታችኋል!…»
ከዚያም ወደ ውዱ ነብያችን ዘወር ብሎ፦ «ወዲያውኑ ከመካከላችን ተለይተህ ወደ ወገንህ ተመለስ!.. እምላለሁ፤ በሕዝቤ መካከል ባትሆን ኖሮ አሁኑኑ አንገትህን በቀላሁ ነበር!..» እስከማለት ድረስ ዕድለ ቢስነቱን አሳየ። በእነዚህ ቃላት የዓለማት ሰይድ በታላቅ ሐዘን ውስጥ ሆነው ግመላቸው ላይ ተቀመጡ። ያ ባለጌ በይሐራ ክቡር ረሱሉላህን ከግመላቸው ላይ ጣላቸው። ይህን ክስተት ያዩ ከሶሓቦች መካከል ደባዓ ቢንት ዓሚር የተባሉ አንዲት ሴት ጮኸው ዘመዶቻቸውን እንዲህ ብለው ተጣሩ፦ «በአላሁ ተዓላ ሐቢብ ላይ ይህ ሲደረግ እንዴት ትፈቅዳላችሁ? ለእኔ ብሎ ረሱሉላህን ከእነዚህ እጅ የሚያድን የለምን?» ከአጎቶቻቸው ልጆች ሦስት ሰዎች ወዲያውኑ ወደ ዕድለ ቢሱ በይሐራ ገሠገሡ። ከበይሐራ ሕዝብ ሁለት ሰዎች ሊረዱት ቢፈልጉም ሌሎቹ በይሐራንና ረዳቶቹን ክፉኛ ደበደቧቸው። ይህን ሁኔታ ይከታተሉ የነበሩት ውዱ ነብያችን ለእርሳቸው ሲሉ ለተዋጉት ለእነዚያ ሦስት ሰዎች፦ «ጌታዬ ሆይ! ለእነዚህ ሰዎች በረከትህን ለግሳቸው»፣ ለበይሐራና ለረዳቶቹ ደግሞ፦ «ጌታዬ ሆይ! እነዚህን ደግሞ ከእዝነትህ አርቃቸው» ብለው ዱዓ አደረጉ።
መልካም ዱዓ ያደረጉላቸው ሰዎች በእስልምና ሲከበሩ፣ ሌሎቹ ደግሞ ከሓዲ ሆነው ሞቱ። የበኑ ዓሚር ጎሳ አባላት ወደ አገራቸው በተመለሱ ጊዜ በመካ ያጋጠማቸውን ሰማያዊ መጻሕፍትን ላነበበ አንድ የጎሳቸው ሽማግሌ ነገሩት። ያ ሰው የክቡር ነብያችንን ስም በሰማ ጊዜ፦ «እናንተ በኑ ዓሚር ሆይ! ምን አደረጋችሁ? ከኢስማዒል ልጆች አንድም ሰው እስከ ዛሬ ድረስ በውሸት ነብይነትን አልተናገረም። እርሳቸው የተናገሩት በእርግጥ እውነትና ሐቅ ነበር። ያመለጣችሁን ይህን ዕድል አሁን መካስ እጅግ ከባድ ነው!..» ብሎ ወቀሳቸው።
ከጂብሪል ጋር ቃል እየተለዋወጡ ሳሉ፣
ረፍረፍ ከፊታቸው መጥቶ ሰላምታ አቀረበላቸው።
ያን ጊዜ የዓለም መሪን ይዞ፣
በዚያው ቅጽበት ወደ ሲድራ ወሰዳቸው።
«እናንተ ሰዎች ሆይ! ላ ኢላሀ ኢለላህ በሉና ዳኑ!» ሐዲስ ሸሪፍ
ኢስራ እና ሚዕራጅ
