በክቡር ነብያችን ተወሱል ማድረግ
በክቡር ነብያችን ሁልጊዜ ተወሱል1 ተደርጓል፤ ከመፈጠራቸው በፊት፣ ከተፈጠሩ በኋላ፣ በዱንያ ሕይወታቸውና ካረፉ በኋላ በበርዘኽ (በቀብር) ዓለም፤ በቂያማ ቀንም ከትንሣኤ በኋላ በዐረሳት ሜዳና በጀነት ይደረጋል። ወሲላ አላሁ ተዓላ በእርሱ ዘንድ ለመቅረብና ጉዳዮች እንዲፈጸሙ ምክንያት ያደረገው ማንኛውም ነገር ነው። በረሱሉል አክረም ተወሱል ማድረግ፣ ማለትም ክቡር ረሱሉላህን በአላሁ ተዓላ ዘንድ ወሲላ ማድረግና እርዳታቸውንና ሸፋዐቸውን መለመን የተፈቀደ ነው። ይህ ሰለፉ ሷሊሒን (ሶሓቦች፣ ታቢዒንና ተበዑ ታቢዒን)፣ ዓሊሞችና ሌሎች ሙስሊሞች ካደረጓቸው ነገሮች ውስጥ ነው። ከሙስሊሞች ማንም ይህን መጥፎ አድርጎ አላየውም። እስካሁን ድረስ ከተበላሸ ዐቂዳ ባለቤቶች በስተቀር እነዚህን የማይቀበል ማንም አልተገኘም። የሰዎች አባት አደም ዐለይሂ ሰላም ወደ ምድር በወረዱ ጊዜ ክቡር ነብያችንን ወሲላ አደረጉ። ይህን ውዱ ነብያችን በአንድ ሐዲስ ሸሪፍ እንዲህ ተረኩ፦ «አደም (ዐለይሂ ሰላም) በስሕተታቸው ምክንያት ከጀነት በወጡ ጊዜ፦ ‹ጌታዬ ሆይ! ለሙሐመድ ክብር ስትል ማረኝ› አሉ። አላሁ ተዓላ፦ ‹አደም ሆይ! ገና ሳልፈጥረው ሙሐመድን እንዴት አወቅኸው?› አለ። አደም (ዐለይሂ ሰላም)፦ ‹ጌታዬ ሆይ! ፈጥረኸኝ ነፍስ በሰጠኸኝ ጊዜ ዓይኖቼን ከፍቼ ስመለከት በዐርሽ ጠርዝ ላይ «ላ ኢላሀ ኢለላህ ሙሐመዱን ረሱሉላህ» ተጽፎ አየሁ። ስሙን ከስምህ ጋር የምትወደው እርሱ ነው› አሉ። አላሁ ተዓላ፦ ‹አደም ሆይ! እውነት ተናገርክ! ከፍጥረታቴ ይበልጥ የምወደው እርሱ ነው። ለእርሱ ክብር ብለህ ምሕረትን ስለለመንክ ማርኩህ› አለ።»2 በአንድ ሪዋያ መሠረት ደግሞ፦ «እርሱ ከዘርህ የሚመጣ ነብይ ነው። እርሱን ባልፈጠርኩ ኖሮ አንተንም ልጆችህንም ባልፈጠርኩ ነበር። እርሱን አማላጅ አድርገህ ስላቀረብክ ማርኩህ፤ ይቅርም አልኩህ።» አለ።3
በዚህ ረገድ በሺዎች የሚቆጠሩ ምሳሌዎች አሉ። ከእነዚህ ጥቂቶቹ ከዚህ በታች ቀርበዋል። ሁለቱም ዓይኖቹ የታወሩ አንድ ሰው ዓይኖቹ እንዲከፈቱ ክቡር ረሱሉላህን ዱዓ እንዲያደርጉለት ጠየቀ። ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን)፦ «ከፈለግህ ዱዓ አደርጋለሁ። ነገር ግን ብትታገሥና ብትችለው ለአንተ የተሻለ ይሆናል።» አሉ። ሰውየውም፦ «ለመታገሥ አቅም አልቀረልኝም። ዱዓ እንዲያደርጉልኝ እማጸናለሁ» አለ። በዚህ ጊዜ፦ «እንግዲያው ውዱእ አድርግና ይህን ዱዓ አንብብ!» አሉት፦
«አላሁመ ኢኒ አስአሉከ ወአተወጀሁ ኢለይከ ቢነቢዪከ ሙሐመዲን ነቢዪ ረሕማ። ያ ሙሐመድ! ኢኒ አተወጀሁ ቢከ ኢላ ረቢ ፊ ሐጀቲ ሃዚሂ፣ ሊቱቅዳ ሊ። አላሁመ ሸፊዕሁ ፊየ።»
ከሐዲስ ዓሊሞች አንዱ የሆኑት ኢማም ነሳኢ ያ ሰው ይህን ዱዓ ባነበበ ጊዜ አላሁ ተዓላ ተቀብሎት ዓይኖቹ እንደተከፈቱ ያሳውቃሉ። ክቡር ረሱሉላህን ወሲላ ስለማድረግ ሰይዲና ዑስማን ኢብኑ ሑነይፍ ይህን ክስተት ይተርካሉ፦ «ዑስማን ኢብኑ ዐፋን ኸሊፋ በነበሩበት ጊዜ ከባድ ችግር የገጠመው አንድ ሰው ኸሊፋው ፊት ለመቅረብ ስላፈረ ጭንቀቱን ለእኔ ነገረኝ። እኔም፦ ‹ወዲያው ውዱእ አድርግ! ወደ መስጂዱ ሰዓዳ ሂድ! ከላይ የተጠቀሰውን ዱዓ አድርግ፤ የምትፈልገውንም ተናገር› አልሁት። ምስኪኑ ሰው ዱዓ ካደረገ በኋላ ኸሊፋው ወዳሉበት ስፍራ ሄደ፤ ወደ ፊታቸውም ቀረበ። ኸሊፋው በገዛ ሙሰላቸው ላይ አስቀምጠውት ችግሩን አዳመጡ፤ ጥያቄውንም ተቀበሉ። ምስኪኑ ሰው ጉዳዩ በድንገት እንደተፈጸመ ባየ ጊዜ ተደስቶ ወደ እኔ መጣና፦ ‹አላሁ ተዓላ በአንተ ይደሰት! አንተ ለኸሊፋው ባትነግራቸው ኖሮ ከችግሬ አልድንም ነበር› አለ። እኔ ከኸሊፋው ጋር የተነጋገርኩ መሰለው።»
«(አደም ሆይ!) እርሱ ከዘርህ የሚመጣ ነብይ ነው። እርሱን ባልፈጠርኩ ኖሮ አንተንም ልጆችህንም ባልፈጠርኩ ነበር። እርሱን አማላጅ አድርገህ ስላቀረብክ ማርኩህ፤ ይቅርም አልኩህ» ሐዲስ ቁድሲ
ሰይዲና ዑመር ኸሊፋ በነበሩበት ጊዜ አንድ ጊዜ ረሃብ ተከሰተ። ከሶሓቦች አንዱ የሆኑት ቢላል ኢብኑል ሐሪስ ወደ ረሱሉላህ ቱርቤ ሄደው፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ኡማዎ በረሃብ ሊጠፉ ተቃርበዋል። ዝናብ እንዲዘንብ ወሲላ እንዲሆኑ እማጸናለሁ» አሉ። ክቡር ረሱሉላህ በዚያ ሌሊት በሕልማቸው ታይተው፦ «ወደ ኸሊፋው ሂድ! ከእኔ ሰላምታ አድርስለት! ለዝናብ ዱዓ ይውጣ!» አሉ። ሰይዲና ዑመር ለዝናብ ዱዓ በወጡ ጊዜ ዝናብ መዝነብ ጀመረ። አላሁ ተዓላ ለሚወዳቸው ሲል ዱዓዎችን ይቀበላል። አላሁ ተዓላ ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላምን እጅግ እንደሚወድ አሳውቋል። ስለዚህ አንድ ሰው «አላሁመ ኢኒ አስአሉከ ቢጃሂ ነቢዪከል ሙስጦፋ» ብሎ ዱዓ ቢያደርግ ዱዓው ውድቅ አይደረግም። ይህም ሆኖ ለጥቃቅን የዱንያ ጉዳዮች ረሱሉላህን ወሲላ ማድረግ ለአደብ ተስማሚ አይደለም። ቡርሃኑዲን ኢብራሂም አል-ማሊኪ እንዲህ አሉ፦ «እጅግ የተራበ አንድ ድሃ ሰው ወደ ሑጅረቱ ሰዓዳ ሄዶ፦ ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ርቦኛል› አለ። ብዙም ሳይቆይ አንድ ሰው መጥቶ ድሃውን ወደ ቤቱ ወስዶ አጠገበው። ድሃው ያደረገው ዱዓ ተቀባይነት እንዳገኘ ሲናገር ሰውየው፦ ‹ወንድሜ! ሚስትህንና ልጆችህን ትተህ ረጃጅም መንገዶችን በችግርና በመከራ አቋርጠህ ረሱሉላህን ለመዘየር መጣህ። ለአንድ ጉርሻ ዳቦ ብለህ በረሱሉላህ ፊት መቅረብ ይገባልን? በዚያ የላቀ ፊት ጀነትንና ዘላለማዊ ጸጋዎችን መለመን ነበረብህ! እዚህ የሚለመኑትን ነገሮች አላሁ ተዓላ አይመልስም› አለው። ረሱሉላህን የመዘየር ክብር ያገኙ ሰዎች በቂያማ ቀን ሸፋዐ እንዲያደርጉላቸው ዱዓ ማድረግ አለባቸው።» አንድ ቀን ኢማም አቡበክር አል-ሙቅሪ ከኢማም ጠበራኒና ከአቡ ሸይኽ ጋር በመስጂዱ ሰዓዳ ተቀምጠው ነበር። ከጥቂት ቀናት ወዲህ ምንም ስላልበሉ እጅግ ርቧቸው ነበር። ኢማም አቡበክር ከዚህ በላይ መቋቋም አቅቷቸው፦ «ርቦኛል፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ!» ብለው ወደ አንድ ማዕዘን ገለል አሉ። ከሰይዶች አንድ ሰው ከሁለት አገልጋዮቻቸው ጋር መጥተው፦ «ወንድሞቼ! ከረሃብ የተነሣ አያቴን ረሱሉላህን እርዳታ ጠይቃችኋል። እንዳጠግባችሁ አዘዙኝ» አሉ። ያመጡትን አብረው በሉ። የተረፈውን ለእነርሱ ትተው ሄዱ። ከእስልምና ዓሊሞች አንዱ የሆኑት አቡ ዐብዱላህ ኢብኑ ኑዕማን አል-መራኩሺ አት-ቲሊምሳኒ (683 / 1284 እ.ኤ.አ.) «ሚስባሑ ዘላም» በተሰኘው ውድ መጽሐፋቸው ክቡር ረሱሉላህን ወሲላ በማድረግ ምኞታቸውን ያገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞችንና ዱዓዎቻቸውን በሰፊው ጽፈዋል። ረሱሉላህን ወሲላ በማድረግ ምኞታቸውን ካገኙት አንዱ ሙሐመድ ኢብኑል ሙንከዲር ናቸው። እንዲህ ይተርካሉ፦ «አንድ ሰው ሰማንያ ወርቅ ለአባቴ ትቶ ወደ ጂሃድ ሄዶ ነበር። ‹እነዚህን ጠብቅልኝ! በጣም ለተቸገረ ሰውም እርዳታ ልትሰጥበት ትችላለህ› ብሎ ነበር። በመዲና ረሃብ ተከሰተ። አባቴ ወርቆቹን በሙሉ በረሃብ ለተጨነቁት አከፋፈለ። የወርቆቹ ባለቤት መጥቶ ጠየቀ። አባቴ፦ ‹ከአንድ ሌሊት በኋላ ና› አለው። ወደ ሑጅረቱ ሰዓዳ ሄዶ እስከ ንጋት ድረስ ረሱሉላህን ተማጸነ። እኩለ ሌሊት ላይ አንድ ሰው መጥቶ፦ ‹እጅህን ዘርጋ!› አለው። አንድ ከረጢት ወርቅ ሰጥቶት ከዚያ ተሰወረ። አባቴ ቤት ውስጥ ወርቆቹን ቆጥሮ ሰማንያ መሆናቸውን ባየ ጊዜ ተደስቶ ወዲያው ለባለቤቱ ሰጠ።»
አቡ ዐብዱላህ አት-ቲሊምሳኒ በዚሁ መጽሐፋቸው በራሳቸው ላይ የደረሰን አንድ ክስተትም እንዲህ ይተርካሉ፦
«በ637 (1239 እ.ኤ.አ.) ዓመት ከተመረጡ ሰዎች ጋር ከሰድር ምሽግ ወጣን። ከእኛ ጋር መንገድ የሚመራን አንድ ሰው ነበር። ለጥቂት ጊዜ ከተጓዝን በኋላ ውኃችን አለቀ። ውኃ መፈለግ ጀመርን። እኔም በዚህ መካከል ለተፈጥሮ ጉዳዬ ገለል አልኩ። በዚህ ጊዜ እጅግ ከባድ እንቅልፍ ወሰደኝ። ‹ሲሄዱ ለማንኛውም ይቀሰቅሱኛል› ብዬ ራሴን መሬት ላይ አኖርኩ።
ስነቃ ራሴን በበረሃው መካከል ብቻዬን አገኘሁት። ጓደኞቼ ረስተውኝ ሄደው ነበር። ከብቸኝነቱ የተነሣ ታላቅ ፍርሃት ያዘኝ። በበረሃው ወደ ቀኝና ወደ ግራ መሄድ ጀመርኩ። የት እንዳለሁና ወዴት እንደምሄድ አላውቅም ነበር። ዙሪያው ሁሉ ዝርግ አሸዋ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ጨለመ። አብረን የምንጓዝበት ቅፍለት ዱካ እንኳ አልነበረም። በሌሊቱ ጨለማ ውስጥ ብቻዬን ነበርኩ። ፍርሃቴ ይበልጥ በረታ። በድንጋጤ ይበልጥ በፍጥነት መሄድ ጀመርኩ። ለጥቂት ጊዜ ከሄድኩ በኋላ እጅግ ተጠምቼ፣ ደክሜና ዝዬ መሬት ላይ ወደቅሁ። ከሕይወቴ ተስፋ ቆርጬ ሞቴ እንደቀረበ ይሰማኝ ጀመር። ሊገለጽ በማይችል ስቃይ ውስጥ ነበርኩ፤ ጭንቀቴና ሐዘኔ የመጨረሻው ጣሪያ ላይ ደርሶ ነበር። በድንገት አንድ ነገር ወደ አእምሮዬ መጣ። በሌሊቱ ጨለማ ውስጥ ኃይሌን ሁሉ አሰባስቤ በቅንነትና በኢኽላስ ለመጨረሻ ጊዜ እንደገና፦ ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ይድረሱልኝ! በአላሁ ተዓላ ፈቃድ እንዲረዱኝ እለምንዎታለሁ!› ብዬ አቃሰትኩ። ቃሌን እንደጨረስኩ አንድ ሰው ሲጠራኝ ሰማሁ። ድምፁ ወደመጣበት አቅጣጫ ስመለከት በሌሊቱ ጨለማ ውስጥ በዙሪያው ብርሃን የሚፈነጥቅ፣ ፍጹም ነጭ ልብስ የለበሰ፣ እስከዚያ ጊዜ አይቼው የማላውቀው አንድ ሰው ሲጠራኝ አየሁ። ወደ እኔ ቀርቦ እጄን ያዘ። በዚያ ቅጽበት ድካሜና ጥማቴ ሁሉ ጠፋ። እንደገና የተወለድኩ ያህል ሆንኩ። ልቤ በድንገት ወደ እርሱ ተሳበ። እጅ ለእጅ ተያይዘን ለጥቂት ጊዜ ሄድን። ከሕይወቴ እጅግ ጣፋጭ ቅጽበቶች አንዱን እያሳለፍኩ እንደሆነ ተሰማኝ። አንድ የአሸዋ ኮረብታ ስናልፍ አብሬ የምጓዝበትን ቅፍለት መብራቶች አየሁ፤ የጓደኞቼንም ድምፅ ሰማሁ። ወደ እነርሱ ቀረብን። የምጋልበው እንስሳ ከሁሉም በስተኋላ እየተከተላቸው ነበር። በድንገት መጥቶ ፊቴ ቆመ። እንስሳዬን ፊቴ ሳይ የደስታ ጩኸት ጮኽኩ። ስጮኽ ከእኔ ጋር የመጣው ሰው እጁን ከእጄ ሳበ። ከዚያም እጄን ይዞ በእንስሳዬ ላይ አወጣኝ። ከዚያም፦ ‹ከእኛ አንድ ነገር የሚለምንንና እርዳታችንን የሚጠይቅን ባዶ እጁን አንመልስም› ብሎ ተመልሶ ሄደ። ያን ጊዜ እርሳቸው ክቡር ረሱሉላህ እንደሆኑ ተረዳሁ። ተመልሰው ሲሄዱ በዙሪያቸው የሚፈነጥቁት ብርሃናት በሌሊቱ ጨለማ ውስጥ ወደ ሰማይ ሲወጡ ይታዩ ነበር። ከዓይኔ በተሰወሩ ጊዜ በድንገት ወደ ልቦናዬ ተመለስኩ። ‹እንዴት የክቡር ረሱሉላህን እጅና እግር አልሳምኩም!› ብዬ ተንገበገብኩ፤ ነገር ግን ጊዜው አልፎ ነበር፤ ዕድሉ አምልጦኝ ነበር።» አቡል ኸይር አል-አቅጠዕ በመዲና ለአምስት ቀን ተርበው ነበር። ወደ ሑጅረቱ ሰዓዳ ሄደው ለረሱሉላህ ሰላምታ አቀረቡ። እንደራባቸው ተናገሩ። ወደ አንድ ማዕዘን ገለል ብለው ተኙ። በሕልማቸው ረሱሉላህ ሲመጡ አዩ። በቀኛቸው አቡበክር ሲዲቅ፣ በግራቸው ዑመር አል-ፋሩቅ፣ ከፊታቸውም ዐሊይ አል-ሙርተዳ ነበሩ።
ሰይዲና ዐሊይ መጥተው፦ «አቡል ኸይር ሆይ! ተነሥ፤ ለምን ተኝተሃል? ረሱሉላህ እየመጡ ነው!» አሉ። ወዲያውኑ ተነሡ። ረሱሉላህ መጥተው ትልቅ ዳቦ ሰጧቸው። አቡል ኸይር እንዲህ ይላሉ፦ «እጅግ ርቦኝ ስለነበር ወዲያውኑ መብላት ጀመርኩ። ግማሹን እንደጨረስኩ ነቃሁ። የቀረውን ግማሽ በእጄ ውስጥ አገኘሁት።»
«አንድ ነገር የጎዳው ሰው ፍጹም ውዱእ አድርጎ ሁለት ረከዓ ይስገድ! ከዚያም፦ ‹ጌታዬ ሆይ! አንተን እለምናለሁ። ለዓለማት እዝነት የሆኑትን ነብይህን ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላምን ወሲላ አድርጌ እማጸንሃለሁ። ሙሐመድ ሆይ! ምኞቴን እንዲቀበል እርስዎን በጌታዬ ዘንድ ወሲላ አደርግዎታለሁ። ጌታዬ ሆይ! እርሳቸውን አማላጄ አድርግልኝ!› ይበል» ሐዲስ ሸሪፍ
በ«ሚስባሑ ዘላም» መጽሐፍም እንዲህ ተተርኳል፦ አሕመድ ኢብኑ ሙሐመድ አስ-ሱፊ እንዲህ ይላሉ፦ «በሒጃዝ በረሃዎች ያለኝን ሁሉ አጣሁ። ወደ መዲና መጣሁ። በሑጅረቱ ሰዓዳ አጠገብ ለረሱሉላህ ሰላምታ አቀረብኩ። በአንድ ማዕዘን ተቀምጬ ተኛሁ። ክቡር ረሱሉላህ ታይተው፦ ‹አሕመድ፣ መጣህን? መዳፍህን ክፈት!› አሉ። መዳፌን በወርቅ ሞሉት። ነቃሁ። እጆቼ በወርቅ ተሞልተው ነበር።» ኢማም ሰምሁዲም «የመዲና ታሪክ» በተሰኘው መጽሐፋቸው በራሳቸው ላይ የደረሰን ክስተት እንዲህ ይተርካሉ፦ «የበሬን ቁልፍ ጣልኩ። ላገኘው አልቻልኩም። ወደ ሑጅረቱ ሰዓዳ ፊት መጥቼ፦ ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ቁልፌን ጣልኩ። ወደ ቤቴ መግባት አልችልም!› አልሁ። በዚያ ቅጽበት አንድ ልጅ መጣ። በእጁ ያለውን ቁልፍ እያሳየ፦ ‹ይህን አገኘሁ። ምናልባት የእርስዎ ይሆን?› አለ።»
ኪሊስሊ ሙስጦፋ ዒሽቂ ኤፈንዲ «Mevârid-i Mecîdiyye» በተሰኘው የታሪክ መጽሐፋቸው እንዲህ ይላሉ፦ «በመካ ሃያ ዓመት ኖርኩ። ስልሳ ወርቅ አጠራቅሜ በ1247 (1831 እ.ኤ.አ.) ከሚስቴና ከልጆቼ ጋር ወደ መዲና መጣን። ገንዘቡ በመንገድ ላይ አለቀ። በአንድ የማውቀው ሰው ቤት በእንግድነት ተቀምጬ ወደ ሑጅረቱ ሰዓዳ መጣሁ። ረሱሉላህን እርዳታ ጠየቅሁ። ከሦስት ቀን በኋላ አንድ ጨዋ ሰው ወዳለንበት ቤት መጥቶ ቤት እንደተከራየልኝ ነገረኝ። ዕቃዎቼን ወደዚያ አስወሰደ። የአንድ ዓመት ኪራይ ከፈለ። ከጥቂት ወራት በኋላ ለአንድ ወር ታምሜ ተኛሁ። በቤት ውስጥ የሚበላም የሚሸጥም ነገር አልቀረም። በባለቤቴ እርዳታ ጣሪያው ላይ ወጥቼ ወደ ረሱሉላህ ቱርቤ ዞሬ ችግሬን ልነግርና እርዳታ ልለምን ፈለግሁ። እጆቼን ባነሣሁ ጊዜ የዱንያ ነገር ለመለመን አፈርኩ። ምንም መናገር አልቻልኩም። ወደ ክፍሌ ወረድኩ። በማግሥቱ አንድ ሰው መጥቶ እገሌ የተባሉ ጨዋ እነዚህን ወርቆች በስጦታ እንደላኩልኝ ነገረኝ። ከረጢቱን ተቀበልኩ። ኑሯችን ቢስተካከልም ከሕመሜ አልዳንኩም ነበር። በሰው እርዳታ ወደ ሑጅረቱ ሰዓዳ ፊት መጥቼ ረሱሉላህን ፈውስ ለመንኩ። ከመስጊዱ ወጥቼ የማንንም እርዳታ ሳልፈልግ ወደ ቤቴ ሄድኩ። ወደ ቤት ስገባ ከሕመሜ ምንም አልቀረም ነበር። ዓይን እንዳይመታኝ ለጥቂት ቀናት በምርኩዝ ተደግፌ ወደ መንገድ ወጣሁ። ነገር ግን ገንዘቡ አልቆ ነበር። ሚስቴንና ልጆቼን በጨለማ ትቼ ወደ መስጂደ ነበዊ መጣሁ። ከዒሻ ሶላት በኋላ ችግሬን ለረሱሉላህ ነገርኳቸው። በመንገድ ላይ የማላውቀው አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ በእጄ አንድ ከረጢት ሰጠኝ። በውስጡ እያንዳንዳቸው ዘጠኝ ኩሩሽ የሚያወጡ አርባ ዘጠኝ ወርቆች ነበሩ። ሻማና የሚያስፈልጉትን ነገሮች ገዝቼ ወደ ቤት መጣሁ።»
የ«Şakâyık-i Nu’mâniyye» መጽሐፍ ትርጉም ሁለተኛው ቅጽ እንዲህ ይላል፦ የኦቶማን መንግሥት የመጀመሪያው ሸይኹል ኢስላምና የዘመናቸው ሙጀዲድ የሆኑት ታላቁ የእስልምና ዓሊም ማውላና ሸምሱዲን ሙሐመድ ኢብኑ ሐምዛ አል-ፈናሪ በዓይኖቻቸው ላይ ሞራ ወጥቶ ማየት አቃታቸው። አንድ ሌሊት ክቡር ረሱሉላህ በሕልማቸው፦ «ሱረቱ ጣሀን ተፍሲር አድርግ!» ባሏቸው ጊዜ፦ «በላቀው ፊትዎ ቁርኣን ከሪምን ተፍሲር ለማድረግ አቅም እንደሌለኝ ሁሉ ዓይኖቼም አያዩም» አሉ። የነብያት ሐኪም የሆኑት ክቡር ረሱሉላህ ከተባረከ ኺርቃቸው አንድ ቁራጭ ጥጥ አውጥተው በተባረከ ምራቃቸው አርጥበው በዓይኖቻቸው ላይ አኖሩት። ሞላ ፈናሪ ነቅተው ጥጡን በዓይኖቻቸው ላይ አገኙት፤ አንሥተውትም ማየት ጀመሩ። አላሁ ተዓላን አመሰገኑ፤ ሹክርም አደረጉ። የጥጡን ክሮች አስቀምጠው ሲያርፉ በዓይኖቻቸው ላይ እንዲደረጉ ኑዛዜ አደረጉ። በ834 (1431 እ.ኤ.አ.) በቡርሳ ባረፉ ጊዜ ኑዛዜያቸውን ፈጸሙላቸው።
ከዐባሲ ኸሊፋዎች አንዱ የሆነው አቡ ጀዕፈር መንሱር በመስጂደ ነበዊ ውስጥ ከኢማም ማሊክ ጋር ይነጋገር ነበር። ኢማም ማሊክ እንዲህ አሉ፦ «መንሱር ሆይ! ይህ መስጂዱ ሰዓዳ ነው! በዝግታ ተናገር! ሐቅ ተዓላ በሱረቱ አል-ሑጁራት በትርጓሜ፦ ‹ድምፃችሁን ከረሱሉላህ ድምፅ በላይ ከፍ አታድርጉ!›4 ብሎ አንድን ቡድን ገስጿል። ‹በረሱሉላህ ዘንድ ድምፃቸውን ዝቅ የሚያደርጉ…›5 በሚለው ክቡር አንቀጽም በዝግታ የሚናገሩትን አወድሷል። ረሱሉላህን ካረፉ በኋላ ማክበር በሕይወት ሳሉ እንደማክበር ነው።» መንሱር አንገቱን ደፍቶ፦ «አቡ ዐብዱላህ ሆይ! ወደ ቂብላ ዞሮ መቆም ነው ወይስ ወደ ቀብሩ ሰዓዳ?» ብሎ ጠየቀ። ኢማም ማሊክ እንዲህ አሉ፦ «ፊትህን ከረሱሉላህ አታዙር! የቂያማ ቀን አማላጅ የሆኑት እኚያ የላቁ ነብይ (የልዑሉ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) በቂያማ ቀን ለአንተና ለአባትህ ለአደም ዐለይሂ ሰላም መዳን ወሲላ ይሆናሉ። ወደ ቀብሩ ሰዓዳ ዞረህ የረሱሉላህን የተባረከች ነፍስ አጥብቀህ ይዘህ ሸፋዐ መለመን አለብህ! በሱረቱ አን-ኒሳ ስልሳ አራተኛው ክቡር አንቀጽ በትርጓሜ እንዲህ ተባለ፦
‹ነፍሶቻቸውን የበደሉ (ራሳቸውን የጎዱ) ሰዎች ወደ አንተ መጥተው አላሁ ተዓላን ምሕረት ቢለምኑ፣ መልዕክተኛዬም ለእነርሱ ምሕረት ቢለምንላቸው አላሁ ተዓላን ተውባን ተቀባይና አዛኝ ሆኖ ያገኙታል።› ይህ ክቡር አንቀጽ ረሱሉላህን ወሲላ የሚያደርጉ ሰዎች ተውባ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ቃል ይገባል።» በዚህ ጊዜ መንሱር ከተቀመጠበት ተነሥቶ በሑጅረቱ ሰዓዳ ፊት ቆመና እንዲህ እያለ መማጸን ጀመረ፦ «ጌታዬ ሆይ! በዚህ ክቡር አንቀጽ መልዕክተኛህን ወሲላ የሚያደርጉትን ሰዎች ተውባ እንደምትቀበል ቃል ገብተሃል። እኔም ወደ ላቀው ነብይህ ከፍተኛ ፊት መጥቼ ምሕረትህን እለምናለሁ። እርሳቸው በሕይወት ሳሉ ምሕረት ለምነው እንደማርካቸው ባሮችህ እኔንም ማረኝ! ጌታዬ ሆይ! ነቢዩ ረሕማ የሆኑትን የላቀውን ነብይህን ወሲላ አድርጌ እማጸንሃለሁ። ከነብያት ሁሉ የላቁት ሙሐመድ ዐለይሂ ሰላም ሆይ! በእርስዎ ተወሱል አድርጌ ጌታዬን ተማጸንኩ። ጌታዬ ሆይ! እኚያን የላቁ ነብይ አማላጄ አድርግልኝ!» በዚህ መልኩ ጀርባው ወደ ቂብላ፣ ፊቱም ወደ ሙዋጀሀቱ ሰዓዳ መስኮት ትይዩ ቆሞ ዱዓ አደረገ። ሚንበሩ ነበዊ በግራው በኩል ነበር። ኢማም ማሊክ ለኸሊፋ መንሱር የሰጡት ምክር በሑጅረቱ ሰዓዳ ፊት ዱዓ የሚያደርጉ ሰዎች እጅግ ንቁዎች መሆን እንዳለባቸው ያሳያል። ለዚያ ስፍራ የሚገባውን አደብና ክብር ማሳየት የማይችሉ ሰዎች በመዲና አል-ሙነወራ ረጅም ጊዜ መቆየታቸው ትክክል እንዳልሆነ ተነግሯል። ከአናቶሊያ ገበሬዎች አንዱ በመዲና አል-ሙነወራ ለዓመታት ኖሮ፣ አግብቶና በሑጅረቱ ሰዓዳ የተወሰነ አገልግሎት ተቀብሎ ነበር። አንድ ቀን የትኩሳት ሕመም ያዘውና አይራን አማረው። «በመንደሬ ብሆን ኖሮ ከእርጎ አይራን አሠርቼ እጠጣ ነበር» የሚል ሐሳብ በልቡ አለፈ። በዚያ ሌሊት ረሱሉላህ ለሸይኹል ሐረም በሕልም ታይተው የዚያ ሰው ሥራ ለሌላ ሰው እንዲሰጥ አዘዙ። ሸይኹል ሐረም፦ «የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ያንን አገልግሎት ከኡማዎ እገሌ እየፈጸመ ነው» ባሉ ጊዜ፦ «ለዚያ ሰው ንገረው! ወደ መንደሩ ሄዶ አይራን ይጠጣ!…» አሉ። በማግሥቱ ይህ ትእዛዝ በተነገረው ጊዜ ገበሬው፦ «እሺ፣ በጄ!» ብሎ ወደ አገሩ ሄደ።
«ነፍሶቻቸውን የበደሉ ሰዎች ወደ አንተ መጥተው አላሁ ተዓላን ምሕረት ቢለምኑ፣ መልዕክተኛዬም ለእነርሱ ምሕረት ቢለምንላቸው አላሁ ተዓላን ተውባን ተቀባይና አዛኝ ሆኖ ያገኙታል» ኒሳ: 64
በልብ ያለፈ ሐሳብ ብቻ ይህን ያህል ጉዳት ካደረሰ፣ አላህ ይጠብቀን፣ በቀልድ እንኳ ቢሆን ያልተገባ ቃል ወይም ከአደብ ጋር የማይስማማ ድርጊት ምን ያህል ታላቅ ጉዳት እንደሚያስከትል ከዚህ መረዳት ይገባል።
የሚወድዎ ምእመን በልቡ ያለው ኢማኑ እርስዎ ነዎት፤
ሐዘን ፈጽሞ አያገኘውም፣ ለሕመሙ መድኃኒቱ እርስዎ ነዎት፤
ሸፋዐዎን ይጠብቃል፣ የልቡ ትእዛዝ እርስዎ ነዎት፤
እርዳታን የሚከጅል በእርግጥ ያገኛል፣ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ።
በክቡር ረሱሉላህ ላይ ሶለዋት ሸሪፍ የማውረድ አስፈላጊነትና ትሩፋት
የክቡር ነብያችን ስም ሲነገር፣ ሲሰማና ሲጻፍ የክብርና የአደብ መግለጫ አድርጎ በእርሳቸው ላይ ሶለዋት ሸሪፍ ማውረድ ከዋነኞቹ ግዴታዎቻችን አንዱ ነው። በቁርኣን ከሪም፣ በሱረቱ አል-አሕዛብ ሃምሳ ስድስተኛው ክቡር አንቀጽ በትርጓሜ እንዲህ ተባለ፦
«በእርግጥ አላሁ ተዓላና መላእክቱ በነብዩ ላይ ሶላት ያወርዳሉ (ክብራቸውንና ማዕረጋቸውን ከፍ ለማድረግ)። እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እናንተም በእርሱ ላይ ሶላትና ሰላም አውርዱ፤ በሙሉ ልባችሁም ለእርሱ ተገዙ።»
የተፍሲር ዓሊሞች በዚህ ክቡር አንቀጽ የተጠቀሰው «ሶላት» የሚለው ቃል ከአላሁ ተዓላ በኩል እዝነትን፣ ከመላእክት በኩል ምሕረት መለመንን፣ ከምእመናን በኩል ደግሞ ዱዓን እንደሚያመለክት አሳውቀዋል። የእስልምና ዓሊሞች ሁሉ በዕድሜ ልክ አንድ ጊዜ ሶለዋት ማውረድ ፈርድ እንደሆነ በአንድ ቃል አሳውቀዋል። ስማቸውን በተናገረ፣ በሰማ፣ ባነበበ ወይም በጻፈ ቁጥር አንድ ጊዜ ማውረድ ዋጂብ ነው፤ ስማቸው ሲደጋገም ደግሞ ሙስተሐብ ነው።
አላሁ ተዓላን አንድ ነገር የሚለምን ሰው መጀመሪያ አላሁ ተዓላን አመስግኖና አወድሶ ከዚያ በኋላ በክቡር ረሱሉላህ ላይ ሶላት ማውረድ አለበት። እንዲህ ያለው ዱዓ ተቀባይነትን ለማግኘት እጅግ የሚገባው ነው። በሁለት ሶላቶች መካከል (በዱዓው መጀመሪያና መጨረሻ) የሚደረግ ዱዓ አይመለስም። ሰይዲና አቡ ጦልሐ እንዲህ ይተርካሉ፦ «ወደ ረሱሉላህ ፊት ገባሁ። ከዚህ በፊት በእርሳቸው ላይ አይቼው የማላውቀውን ደስታና እርካታ አየሁ። ምክንያቱን ስጠይቅ፦ ‹እንዴት አልደሰት? አሁን ጂብሪል (ዐለይሂ ሰላም) የምሥራች አመጡ፤ አላሁ ተዓላ እንዲህ ይላል፦ ከኡማህ አንድ ሰው በአንተ ላይ አንድ ሶለዋት ቢያወርድ አላሁ ተዓላ በምትኩ በእርሱ ላይ አሥር ሶለዋት ያወርዳል።› አሉ።»6
በዚህ ጉዳይ ላይ ካሉት ሐዲሶች ሸሪፍ አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦
«ስሜ በእርሱ ዘንድ ተጠቅሶ በእኔ ላይ ሶላትና ሰላም የማያወርድ ሰው አፍንጫው በአፈር ይታሽ። የረመዳን ወር ገብቶ ወንጀሎቹን ሳያስምር የረመዳን ወር የሚወጣበት ሰውም አፍንጫው በአፈር ይታሽ። የአባቱንና የእናቱን እርጅና ደርሶ ውዴታቸውን አግኝቶ ጀነት መግባት ያልቻለ ሰውም አፍንጫው በአፈር ይታሽ።»
«ስሜ በእርሱ ዘንድ ተጠቅሶ በእኔ ላይ ሶላትና ሰላም የማያወርድ ሰው ከንፉጋን ሁሉ የባሰ ንፉግ ነው።» ሰይዲና አቡ ሑመይድ አስ-ሳዒዲ እንዲህ ያሳውቃሉ፦ «ከሶሓቦች አንዳንዶቹ ክቡር ረሱሉላህን፦ ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! በእርስዎ ላይ ሶላትና ሰላም እንዴት እናውርድ?› ብለው ጠየቁ። ክቡር ረሱሉላህ እንዲህ አሉ፦ ‹አላሁመ ሶሊ ዐላ ሙሐመዲን ወአዝዋጂሂ ወዙሪያቲሂ ከማ ሶለይተ ዐላ ኢብራሂመ ወባሪክ ዐላ ሙሐመዲን ወአዝዋጂሂ ወዙሪያቲሂ ከማ ባረክተ ዐላ ኢብራሂመ ኢነከ ሐሚዱን መጂድ በሉ።›»7
አንዳንድ ሶለዋት ሸሪፎች እንዲህ ናቸው፦
«ዐለይሂ ሰላም»።
«ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም»።
«ዐለይሂ ሶላቱ ወሰላሙ ወተሒያ»።
«አላሁመ ሶሊ ዐላ ሰይዲና ሙሐመድ»።
«አላሁመ ሶሊ ዐላ ሙሐመዲን ወዐላ ኣሊሂ ወሶሕቢሂ አጅመዒን»።
«ዐለይሂ ወዐላ ጀሚዒ ሚነ ሶለዋቲ አተሙሃ ወሚነ ተሒያቲ አይመኑሃ»።
«አላሁመ ሶሊ ዐላ ሙሐመዲን ወዐላ ኣሊ ሙሐመድ፣ ከማ ሶለይተ ዐላ ኢብራሂመ ወዐላ ኣሊ ኢብራሂም…»
አንድ ሰው እንዲህ ተረከ፦ ከጓደኞቼ አንዱ በላከልኝ ደብዳቤ የረሱሉላህ የተባረከ ስም በተጠቀሰበት ስፍራ ሁሉ «ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ተስሊመን ከሲረን ከሲራ» ብሎ ጽፎ ነበር። ባየሁት ጊዜ ምክንያቱን ስጠይቀው እንዲህ አለ፦ «በወጣትነቴ የሐዲስ መጻሕፍትን እጽፍ ነበር። የረሱሉላህን የተባረከ ስም በጻፍኩ ቁጥር ሶለዋቱን አልጽፍም ነበር። በሕልሜ የዓለማት ሰይድን አይቼ ወደ እርሳቸው ቀረብኩ። የተባረከ ፊታቸውን ከእኔ አዞሩ። ወደ ሌላው ጎናቸው ሄድኩ፤ እንደገና አዞሩ። ፊት ለፊታቸው ቆሜ፦ ‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ፊትዎን ከእኔ ለምን ያዞራሉ?› አልኋቸው። ‹ምክንያቱም አንተ በመጽሐፍህ ስሜን በጻፍክ ጊዜ በእኔ ላይ ሶላት አላወረድክም!› አሉ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተባረከ ስማቸውን ሁልጊዜ ከሶላት ጋር እጽፋለሁ።»
በሐዲሶች ሸሪፍ እንዲህ ተባለ፦
«በእኔ ላይ አንድ ጊዜ ሶላት ያወረደ ሰው አላሁ ተዓላ በእርሱ ላይ አሥር ጊዜ ሶላት (እዝነት) ያወርዳል፣ አሥር ወንጀሎቹን ይምራል፣ ደረጃውንም አሥር እጥፍ ከፍ ያደርጋል።»
«በቂያማ ቀን ለእኔ ይበልጥ ቅርብ የሆነውና ሸፋዐዬ ይበልጥ የሚገባው በእኔ ላይ ብዙ ሶላትና ሰላም የሚያወርደው ሰው ነው።» ሐቅ ተዓላ ለሙሳ ዐለይሂ ሰላም እንዲህ አለ፦ «ሙሳ ሆይ፣ ለአንደበትህ ከቃልህ፣ ለልብህ ከሐሳብህ፣ ለአካልህ ከነፍስህ፣ ለዓይንህ ከብርሃኑ ይበልጥ ቅርብ እንድሆን ትፈልጋለህን?» «አዎ፣ ጌታዬ ሆይ!» ባሉ ጊዜ አላሁ ተዓላ፦ «እንግዲያው በሙሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ላይ ብዙ ሶለዋት አውርድ።» አለ። ከዚያም፦ «ሙሳ ሆይ፣ በቂያማ ቀን ጥም እንዳያገኝህ ትፈልጋለህን?» አለ። «አዎ፣ ጌታዬ ሆይ!» ባሉ ጊዜ አላሁ ተዓላ፦ «እንግዲያው በሙሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ላይ ብዙ ሶለዋት አውርድ።» አለ።8
ክቡር ነብያችን እንዲህ አሉ፦
«በቂያማ ቀን በየስፍራው ሁሉ ከእናንተ መካከል ለእኔ ይበልጥ ቅርብ የሆነው በዱንያ በእኔ ላይ ብዙ ሶለዋት የሚያወርደው ነው። በጁሙዓ ቀንና በጁሙዓ ሌሊት በእኔ ላይ መቶ ሶለዋት ያወረደን ሰው አላሁ ተዓላ መቶ ጉዳዮቹን ይፈጽምለታል፤ ሰባው የአኺራ፣ ሠላሳው የዱንያ ጉዳዮች ናቸው። ከዚያም አላሁ ተዓላ እነዚህን ሶላቶች በአንድ መልአክ ወደ ቀብሬ ያስመጣቸዋል። ወደ እናንተ እንደሚመጣ ስጦታ ይሆናሉ። ያ መልአክ የላከውን ሰው ስም፣ ዘርና ጎሳ ይነግረኛል። በእኔ ዘንድ ባለው ነጭ ገጽ ላይ ያሰፍረዋል። ከሞትኩ በኋላ ማወቄ በሕይወት ሳለሁ እንደማውቀው ነው።»9
«በእኔ ላይ አንድ ጊዜ ሶላት ያወረደ ሰው አላሁ ተዓላ በእርሱ ላይ አሥር ጊዜ ሶላት (እዝነት) ያወርዳል፣ አሥር ወንጀሎቹን ይምራል፣ ደረጃውንም አሥር እጥፍ ከፍ ያደርጋል» ሐዲስ ሸሪፍ
«ሐሙስ ቀን በሆነ ጊዜ አላሁ ተዓላ የብር መዝገቦችንና የወርቅ ብዕሮችን የያዙ መላእክትን ይልካል። በሐሙስ ቀንና በጁሙዓ ሌሊት በነብዩ ላይ ብዙ ሶላት የሚያወርዱትን ይጽፋሉ።» «ሁለት ሙስሊሞች ተገናኝተው ቢጨባበጡና በነብዩ ላይ ሶለዋት ቢያወርዱ ከመለያየታቸው በፊት የቀደሙትም የኋለኞቹም ወንጀሎቻቸው ይማርላቸዋል።» «ከእናንተ አንዱ ወደ መስጊድ በገባ ጊዜ ለነብዩ ሰላምታ ያቅርብ፤ ‹ጌታዬ ሆይ! ከሰይጣን ጠብቀኝ!› ይበል።»10
በአንድ ዘገባ ደግሞ፦ «ከመስጊድ ሲወጣ ‹አላሁመ ኢኒ አስአሉከ ሚን ፈድሊክ› ይበል።» ተብሏል።
የዱዓ መጀመሪያ ለአላሁ ተዓላ ውዳሴ (ሐምድ) እና በረሱሉላህ ላይ ሶለዋት ካልሆነ ዱዓው ከመጋረጃ በስተጀርባ ይቀራል። መጀመሪያው ሐምድና ሶለዋት የሆነ ዱዓ ተቀባይነት ያገኛል። በረሱሉላህና በቤተሰባቸው (ኣል) ላይ ሶለዋት እስካልተወረደ ድረስ በዱዓውና በሰማይ መካከል መጋረጃ አለ። ሶለዋት በተወረደ ጊዜ ይህ መጋረጃ ይቀደዳል፤ ዱዓውም ወደ ሰማይ ይወጣል። ሶለዋት ካልተወረደ ዱዓው ተመልሶ ይመጣል።
በአንድ ጉባኤ ውስጥ አላሁ ተዓላ ካልታወሰና በረሱሉላህ ላይ ሶላት ካልተወረደ በዚያ ባሉት ሰዎች ላይ አለንጋ ይንጠለጠላል፤ ከሻ ይቀጣቸዋል፣ ከሻም ይምራቸዋል።
«ጆሮው የሚያቃጭልበት ሰው እኔን ያስታውስ፤ በእኔም ላይ ሶላት ያውርድ።»
«አንድን ሥራ ለመሥራት ያሰበ ሰው በዚያ ጉዳይ ላይ ይመካከር። አላሁ ተዓላ በሥራው ቅኑን መንገድ ይለግሰዋል። አንድ ሰው አንድን ቃል ለመናገር ፈልጎ ቢረሳው በእኔ ላይ ሶላት ያውርድ። ምክንያቱም በእኔ ላይ በሚያወርደው ሶላት ውስጥ ለቃሉ ምትክ አለ። ያስታውሰው ዘንድ ይከጀላል።»11
«በአላህ ስምና በእኔ ላይ በሚወርድ ሶላት ያልተጀመረ መልካም ሥራ ውስጥ መልካም ነገር የለም፤ በረከቱም ሁሉ ተወግዷል።»12 ከእስልምና ታላላቆች አንዱ የሆኑት አቡ ሐፍስ ካጊዲ ባረፉ ጊዜ አንድ ሰው በሕልሙ አይቷቸው፦ «አላሁ ተዓላ ምን አደረገልዎት?» ብሎ ጠየቃቸው። «እዝነቱን ሰጥቶኝ ምሕረት አደረገልኝ፤ ጀነትም አስገባኝ» አሉ። «በምን ምክንያት?» ብሎ በጠየቀ ጊዜ እንዲህ ብለው መለሱ፦ «በመላእክት መካከል አቆሙኝ። ወንጀሎቼንና በረሱሉላህ ላይ ያወረድኳቸውን ሶለዋቶች አመዛዘኑ፤ ሶለዋቶቼ እንደሚበዙ አገኙ። አላሁ ተዓላም እንዲህ አላቸው፦ ‹መላእክቴ ሆይ! ሥራችሁ ተጠናቋል። ሌላ ሒሳብ አትጠይቁት። ወደ ጀነቴ ውሰዱት!›»
ከሰለፎች አንዱ እንዲህ ይተርካሉ፦ «አብረን ሐዲስ የተማርን አንድ ጓደኛዬ አረፈ። በሕልሜ አረንጓዴ የጀነት ልብሶችን ለብሶ አየሁት። ምክንያቱን በጠየቅሁት ጊዜ፦ ‹በማየው ሐዲስ ሁሉ ከረሱሉላህ ስም ጎን «ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም» ብዬ እጽፍ ነበር። ሐቅ ተዓላ ምንዳውን በዚህ መልኩ ሰጠኝ› አለ።»
ከሰለፎች ሌላው ደግሞ እንዲህ ይተርካሉ፦ «ጸሐፊ የነበረ አንድ ጎረቤቴ ሞተ። በሕልሜ አየሁትና አላሁ ተዓላ ምን እንዳደረገለት ጠየቅሁት። አላሁ ተዓላ ምሕረት እንዳደረገለት ነገረኝ። ምክንያቱን በጠየቅሁት ጊዜ፦ ‹የረሱሉላህን ስም በጻፍኩ ቁጥር «ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም» የሚለውን ቃል አብሬ እጽፍ ስለነበር ነው› አለ።» አቡ ሱለይማን አድ-ዳራኒ እንዲህ ይተርካሉ፦ «ሐዲስ ስጽፍ የተከበረ ስማቸውን በጻፍኩ ቁጥር «ሰለላሁ ዐለይሂ» ብዬ እጽፍ ነበር፤ «ወሰለም» የሚለውን ቃል ግን አልጽፍም ነበር። በሕልሜ አየኋቸው፤ እንዲህም አሉኝ፦ ‹አቡ ሱለይማን ሆይ! በሐዲስ ውስጥ ስሜን በጻፍክ ጊዜ ከሶላቱ ጋር «ወሰለም»ንም ጻፍ። እርሱ አራት ፊደላት ነው። ለእያንዳንዱ ፊደል አሥር ምንዳ አለ። ካልጻፍከው አርባ ምንዳ ትተዋለህ ማለት ነው።›»
የሌላ ሰውም ልማድ ይኸው ነበር። ረሱሉላህ በሕልሙ፦ «ምን ሆነህ ነው በእኔ ላይ ሶላትን አሟልተህ የማትጽፈው?» አሉት።
አቡበክር ሲዲቅ እንዲህ አሉ፦ «መርሳትን የሚፈራ ሰው በረሱሉላህ ላይ ብዙ ሶለዋት ያውርድ።»
ከሷሊሖች ታላላቆች አንዱ የሆኑት ሙሐመድ ኢብኑ ሰዒድ ኢብኑ ሙጠሪፍ እንዲህ ይተርካሉ፦ «በየሌሊቱ ለመተኛት ስዘጋጅ የተወሰነ ቁጥር ሶላት አወርድ ነበር። አንድ ሌሊት በሕልሜ ረሱሉላህ መጡ። ወደ ውስጥ ገቡ። ክፍሌ በኑር ተሞላ። ከዚያም ወደ እኔ መጥተው፦ ‹በእኔ ላይ ብዙ ሶለዋት የሚያወርደውን ያንን አፍህን አምጣ፤ ልሳመው› አሉ። እኔም አፌን ለማቅረብ አፍሬ ጉንጬን ዘረጋሁ። በተባረከ አፋቸው ሳሙት። በደስታ ነቃሁ። ክፍሌ በሚስክ መዓዛ ተሞልቶ አገኘሁት። ያ መልካም መዓዛ ለስምንት ቀን ከጉንጬ አልጠፋም።» ከሰለፍ ታላላቆች አንዱ የሆኑት ኸላድ ኢብኑ ከሲር ባረፉ ጊዜ ከራሳቸው ሥር፦ «ይህ የኸላድ ኢብኑ ከሲር ከጀሀነም የመዳን ሰነድ ነው» የሚል የተጻፈበት ወረቀት አገኙ። ዘመዶቻቸውን፦ «ሥራቸው ምን ነበር?» ብለው ጠየቁ። «በየጁሙዓው ቀን ሶለዋት ያወርዱ ነበር» አሉ። በሸይኽ ዐይኒ «ዘይኑል መጃሊስ» እንዲህ ተጽፏል፦ ረሱሉላህ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) እንዲህ አሉ፦ «በቂያማ ቀን ሦስት የሰዎች ቡድኖች ከእርሱ ጥላ በስተቀር ሌላ ጥላ በሌለበት በዐርሽ ሥር ይሆናሉ።» «እነርሱ እነማን ናቸው?» ብለው ጠየቁ። «ኡማዬን ከችግር የሚያወጣ፣ ሱናዬን ሕያው የሚያደርግ እና በእኔ ላይ ብዙ ሶለዋት የሚያወርድ ነው» አሉ።
ሸይኽ አቡ ሙሳ ደሪሪ እንዲህ ይተርካሉ፦ «በባሕር ላይ አውሎ ነፋስ ያዘን። ሁሉም ሞትን ፈርቶ ያለቅስ ነበር። በዚያ ሁኔታ ውስጥ እንቅልፍ ወሰደኝ። በሕልሜ ረሱሉል አክረምን አየሁ። ‹በመርከቡ ላይ ላሉት ሰዎች ንገራቸው፤ ሺህ ጊዜ፦ አላሁመ ሶሊ ዐላ ሰይዲና ሙሐመዲን ወዐላ ኣሊ ሰይዲና ሙሐመድ፣ ሶላተን ቱንጂና ቢሃ ሚን ጀሚዒል አሕዋሊ ወል ኣፋት፣ ወተቅዲ ለና ቢሃ ጀሚዐል ሐጃት፣ ወቱጠሂሩና ቢሃ ሚን ጀሚዒ ሰይአት፣ ወተርፈዑና ቢሃ ዒንደከ አዕለ ደረጃት፣ ወቱበሊጉና ቢሃ አቅሰል ጋያት ሚን ጀሚዒል ኸይራቲ ፊል ሐያቲ ወበዕደል መማት ይበሉ› አሉ። ገና ሦስት መቶ ጊዜ እንዳነበብነው አውሎ ነፋሱ ጸጥ አለ፤ እኛም ዳንን።» ይህን ሶላት በእያንዳንዱ አስፈላጊ ጉዳይ፣ በእያንዳንዱ መከራ፣ ጥፋትና የመሬት መንቀጥቀጥ ጊዜ እንዲነበብ ተመክሯል።
የሰው ልጆች ኩራት ሆይ! ሌትም ቀንም በአንደበቴ ለዚያች የተባረከች ነፍስዎ ሶላትና ሰላም አለ።
በታማኝ መጻሕፍት ውስጥ ሶላት እንዴት እንደሚወርድ የሚገልጹ ከአርባ በላይ ሐዲሶች አሉ።
ከእነርሱም አንዱ የሚከተለው ነው፦
«ጆሮው የሚያቃጭልበት ሰው እኔን ያስታውስ፤ በእኔም ላይ ሶላት ያውርድ» ሐዲስ ሸሪፍ
አላሁመ ሶሊ ዐላ ሙሐመዲን ወዐላ ኣሊ ሙሐመድ፣ ከማ ሶለይተ ዐላ ኢብራሂመ ወዐላ ኣሊ ኢብራሂም፣ ወባሪክ ዐላ ሙሐመዲን ወዐላ ኣሊ ሙሐመድ፣ ከማ ባረክተ ዐላ ኢብራሂመ ወዐላ ኣሊ ኢብራሂም፣ ኢነከ ሐሚዱን መጂድ።
አላሁመ ሶሊ ወሰሊም ወባሪክ ወርሐም ዐላ ሰይዲና ሙሐመዲን ሁወ ሰይዱል ዐረቢ ወል ዐጀም።
ወኢማሚ መከተል ሙከረመቲ ወል መዲነቲል ሙነወረቲ ወል ሐረም። ዐለመል ኢንሳነ ማ ለም የዕለም።
አስሉሁ ኑሩን ወነስሉሁ ኣደም።
በዕሱሁ ሙአኸሩን ወኸልቁሁ ሙቀደም።
ኢስሙሁሽ ሸሪፉ መክቱቡን ዐለል ለውሒል መሕፉዚ ቢያቁቲል ቀለም።
ወጂስሙሁሽ ሸሪፉ መድፉኑን ፊል መዲነቲል ሙነወረቲ ወል ሐረም።
ያ ለይተ አክተሒሉ ቱራበለዚ ተሕተል ቀደም።
ፈጡባ ሱመ ጡባ ሊመን ደዓ ወተቢዐሁ ወሊመን አስለመ ሷሒበሽ ሸፋዐቲ ሊል ዓለሚን።
ቃኢለን ያ ረቢ! ሰሊም ኡመቲ፣ ኡመቲ፣ ዋ ኡመታ ያ ዘል ሉጥፊ ወል ከረም።
ፈዩናዲል ሙናዲ ሚን ቂበሊር ረሕማን፣ ቀቢልቱ ሸፋዐተከ ያ ነቢየል ሙሕተረም።
ኡድኹሉል ጀነተ ላ ኸውፉን ዐለይኩም ወላ ሑዝኑን ወላ አለም።
ሱመ ረዲየላሁ ተዓላ ዐን አቢ በክሪን ወዑመረ ወዑስማነ ወዐሊዪን ዚል ከረም።
ወሶለላሁ ዐላ ሰይዲና ሙሐመዲን ወል ሐምዱ ለከ ያ ረበል ዓለሚን።
ቢሑርመቲ ሰይዲል ሙርሰሊን።
የንጋት ነፋስ ጸጉራቸውን በዳሰሰ ጊዜ፣
አየሩ በሚስክና በዐንበር ይሞላ ነበር።
በሌሊት ከዕንቁ ጥርሶቻቸው ብርሃን የተነሣ፣
መርፌ ቢወድቅ እንኳ ይገኝ ነበር፣ መምህር ሆይ።
ከኑር ደረታቸው የተነሣ በጨለማ ሌሊቶች ወጣቶችም ሽማግሌዎችም መንገዳቸውን ይሄዱ ነበር።
ያ የሐቁ ተወዳጅ በጣታቸው
ወደ ጨረቃ በጠቆሙ ጊዜ ለሁለት ተሰነጠቀች።
ቢያልባቸው እያንዳንዱ ላባቸው ጽጌረዳ ይሆን ነበር፣
ከላባቸውም ጽጌረዳዎችን በደስታ ይለቅሙ ነበር።
ያ የዓለም መሪ የተምር ዛፍ ተከሉ፣
በተከሉበትም ሰዓት ወዲያው ፍሬ ሰጠ።
ተአምራታቸው እስከ መሕሸር ያለማቋረጥ ቢነገር፣
ስንት መሕሸር ቢመጣ እንኳ ፍጻሜ አይደርስለትም።
ከእሳት መዳንን ብትሹ፣
በፍቅርና በናፍቆት ሶላትን አውርዱ!
አስ-ሶላቱ ወሰላሙ ዐለይከ ያ ረሱለላህ!
አስ-ሶላቱ ወሰላሙ ዐለይከ ያ ሐቢበላህ!
አስ-ሶላቱ ወሰላሙ ዐለይከ ያ ኑረ ዐርሺላህ!
